ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር እንዳለበት ተገለጸ

ግንቦት 09/2013 (ዋልታ) – ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚያደርሰውን ሰብአዊና ማህበራዊ ቀውስ ለመግታት የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ።

ህገ ወጥ የሰዎች ፍልሰትን ለመከላከል የአማራ ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ በላሊበላ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በመድረኩ እንዳሉት፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት የወጡ አዋጆችን መሬት ላይ በማውረድ በቁርጠኝነት መስራት ይገባል።

ድርጊቱ ለአስከፊ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት የሚዳርግ መሆኑን በየጊዜው በሚያጋጥሙ አደጋዎች መገንዘብ እንደሚቻል ጠቅሰዋል።

በህግ ወጥ መንገድ ሰዎችን ከሀገር የማስወጣት ተግባር ከሃሳብ እስከ ተግባር እንዲሁም ከመነሻ እስከ መዳረሻ በተወሳሰበ ወንጀል የሚከወን በመሆኑ ቁጥጥርና ክትትሉን አስቸጋሪ እንዳደረገው ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።

ዜጎች በበረሃ በሚያደርጉት ጉዞ በውሃ ጥምና በረሃብ ከመሰቃየት ባሻገር በውቅያኖስ ሰምጠው የሚቀሩ መኖራቸው ችግሩን አሳሳቢ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

በአጋጣሚ የተሻገሩ ቢኖሩ እንኳ ምቹ የስራ ሁኔታ፣ የመኖሪያና ለሰው ለጅ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን የማግኘት መብት ስለማይኖራቸው አኗኗራቸው በአስከፊ ሁኔታ መሆኑን አመልክተዋል።

መንግስት ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት ህጋዊ የስራ ስምሪት አዋጅ በማውጣት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው ፍላጎቱ ያላቸው ዜጎች ከህገ ወጥ ይልቅ ይህን መልካም እድል መጠቀም እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ለ44ሺህ ዜጎች ህጋዊ መስመሩን ተከትለው የውጭ የስራ እድል የተፈጠረላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም ወጣቱ ወደ ውጭ ሃገር ማማተር ብቻ ሳይሆን መንግስት ያመቻቸለትን የስራ እድል በመጠቀም በአካባቢውን ጸጋ ሰርቶ ለመበልጸግ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ድርጊቱ የሚያደርሰውን ሰብአዊና ማህበራዊ ቀውስ ለመግታት የባለድርሻ አላካት ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሚኒስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል።

በምክትል ርዕሰ ማስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ በበኩላቸው፣ የአማራ ክልል የሀገሪቱን ብቻ ሳይሆን የጎረቤት ሀገራት ስደተኞች መተላለፊያ መሆኑን ተናግረዋል።

በህገ ወጥ ደላሎች አማካኝነት የሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ሌሎች ጎረቤት ሀገራት ስደተኞች ወደ ሌሎች ሀገራት ለመሄድ የሚሞክሩት በክልላችን በመተላለፍ ነው ብለዋል።

ይህን ቀጣናዊ ችግር ለመግታት ወጣቱን በማስተማርና አስተሳሰቡን በመለወጥ፣ አጥፊዎችን ወደ ህግ በማቅረብና በኬላ አካባቢዎች ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።