ምርትን በመያዝ ለፖለቲካ መጠቀሚያ በሚያደርጉ ላይ ቁጥጥር እንደሚደረግ ተገለጸ

ጃንጥራር ዓባይ

መጋቢት 3/2015 (ዋልታ) ምርትን በመያዝ ለሌላ የፖለቲካ ቀውስ መጠቀሚያ ለማድረግ የሚደረጉ ሙከራዎች ላይ መንግሥት ጠንካራ ቁጥጥር እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የስራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ ከጥር ወር አጋማሽ በኋላ ያለውን ሁኔታ በአጠቃላይ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰር በሕገ ወጥ መንገድ  ዋጋን በማናር ሕዝብን ለማነሳሳት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸው የሚካድ አይደለም ብለዋል።

ምርትን ይዞ በማቆየት እና የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የፖለቲካ ቀውስ መጠቀሚያ በሚያደርጉ አካላት ላይ መንግሥት ጠንካራ ቁጥጥር እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

አሁን ላይ የተፈጠረውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በአዲስ አበባ ከተማ ያለው ኅብረተሰብ ሰፊ የጤፍ ፍጆታ ይፈልጋል ያሉት ምክትል ከንቲባው ይህንን ለማሟላት ኅብረት ሥራ ማኅበራት በተጠናከረ መንገድ ምርት ወደ ከተማ እንዲገባ ለማድረግ የሚያስችል ትስስር ፈጥረዋል ብለዋል።

ለዚህም ከንግድ፣ ከገቢ፣ ከፖሊስ፣ ከደንብ አስከባሪዎችና ከማህበራት የተውጣጣ ግብረ-ኃይል የተደራጃ ሲሆን ግብረ-ኃይሉ በዋናነት አቅርቦትን ማሳለጥና ሕገወጥነትን የመቆጣጠር ተልዕኮዎችን ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ምርት ወደ ገበያ እንዳይወጣ የማድረግ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፤ በሌላ መንገድ ንግድ ላይ ያሉና ድለላ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት እየገዙ የማከማቸትና ወደ ግብይት እንዳይገባ የማድረግ ሁኔታዎች አጋጥመዋል ያሉት ምክትል ከንቲባው በወፍጮ ቤቶች ብዙ ምርቶችን በመያዝና ወደ ግብይት የሚገባውን ውስን በማድረግ ዋጋ ሲወደድ ለመሸጥ የሚደረጉ ፍላጎቶችና ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውንም አንስተዋል።

ኬላዎችን በመዝጋት ምርት በነጻ እንዳይንቀሳቀስ እና ግብይቱ እንዳይሳለጥ የሚደረግበት ሁኔታ መፈጠሩን በመጥቀስ፤ ይህም በመዲናዋ የምርት እጥረት እንዲኖር ማድረጉን መናገራቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

“ከክልሎች ጋር ባለን ግንኙነት በዚህ ዓመት በቂ ምርት መኖሩንና ለፍጆታ የሚሆን ምርት እንዳለ መረጃው አለን” ያሉት ምክትል ከንቲባው ነገር ግን ከተማ ውስጥ ላለው ኅብረተሰብ ምርቱን አቅርቦ ከመሸጥ ይልቅ በኮንትሮባንድ እንዲወጣ የሚደረግባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ገልጸዋል።

ችግሩን ለመፍታት ከፌዴራል መንግሥትና ከክልሎች ጋር በመነጋገር በሕገወጥ መንገድ የተዘጉ ኬላዎች እየተከፈቱና ምርት የሚገባበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁመው ምርት በብዛት ወደ መዲናዋ ሲገባ የናረው የጤፍ ዋጋ ቅናሽ እንደሚኖረው ተናግረዋል።