ምርጫው ስልጣን የሞት ሽረት ጉዳይ ነው የሚለውን አስተሳሰብ የሰበረ ነው – አቶ እርስቱ ይርዳ


ሰኔ 20/2013 (ዋልታ) –
6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ላደረጉ አካላት የምስጋና ፕሮግራም በቡታጅራ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ 6ኛዉ ሀገራዊ ምርጫ በሰላም መጠናቀቁን አስመልክቶ በቡታጅራ ከተማ በተዘጋጀ የምስጋና ፕሮግራም ላይ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም በነበሩት የምርጫ ሂደቶች ስልጣን የሞት ሽረት ጉዳይ ነው የሚለዉን አስተሳሰብ ያስቀረ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ አድርጋ ምንም አይነት የጸጥታ ችግር ሳይኖር በስኬት ማጠናቀቅ የቻለች ሀገር በመሆኗ የተሰማቸዉን ልባዊ ደስታ በራሳቸዉና በክልሉ መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።
ምርጫዉ በስኬት እንዲጠናቀቅ የሀገራችን ህዝቦች አኩሪ ታሪክ ሰርተዋል ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዴሞክራሲያዊ መንገድ መንግስት መምረጥ እንደሚቻል አብነት የሆነ ስራ መሰራቱንም አብራርተዋል።
ምርጫ የግጭትና የጭቅጭቅ ምንጭ ከመሆን ያለፈና ህዝቡ የሚፈልገዉን ፓርቲ እና ግለሰብ መምረጥ የቻለበት አጋጣሚ መፈጠሩን ተናግረዋል።
እንደ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ ህዝባችንን የበለጠ ማገልገል እንድንችል ትልቅ የቤት ስራ የተረከብንበት ወቅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
ምርጫዉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የላቀ አስተዋጽኦ ላደረጉ ለምርጫ ቦርድ አባላት ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ለጸጥታ አካላት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ለተሰማሩ ወጣቶች እንዲሁም ወቅታዊ መረጃዎችን ለህዝብ እንዲደርስ ላደረጉ የሚዲያ አካላት እና ለመላው ህዝብ ምስጋና አቅርበዋል።
እንደ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ ከምርጫ በኋላ ቀሪ የልማት ስራዎች ላይ በማተኮር ይሰራልም ብለዋል።
በቀጣይ ጊዜያት ባለፈዉ የበልግ ልማት ስራዎች ላይ ባጋጠመ የዝናብ እጥረት ምክንያት ያላሳካናቸዉን የመኸር ግብርና ስራዎች ላይ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ እንድንችል በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ስራችንን ማጠናከር ደግሞ ሌላው አብይ ጉዳይ ነው ሲሉም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ መግለጻቸውን ከደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡