በፍራንክፈርት ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የ16 ሺህ ዩሮ ቦንድ ግዥ ተፈፀመ


ሰኔ 20/2013 (ዋልታ) –
በጀርመን ፍራንክፈርት በተካሄደ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብር ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የ16 ሺህ ዩሮ ቦንድ ግዥ መፈፀሙን እና የ67 ሺህ ዩሮ ቦንድ ግዢ ቃል መገባቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብሩ ፍራንክፈርት በሚገኘው ኢፌዴሪ ቆንስላ ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሲሆን በጀርመን ፍራንክፈርት አከባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በባለሀብቶች እና ምሁራን ተሳትፈውበታል።
በጀርመን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አራት ካርጎ ኤጀንቶች እያንዳንዳቸው የ3 ሺህ ዩሮ በድምሩ የ12 ሺህ ዩሮ ቦንድ ግዢ የፈጸሙ መሆኑ እና በቀጣይም የ55 ሺህ ዩሮ ቦንድ ለመግዛት ቃል መግባታቸው ተገልጿል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙ አንድ በጀርመን ፍራንክፈርት የሆቴል ባለቤት ትውልደ የኢትዮጵያዊ የ10 ሺህ ዩሮ የሕዳሴው ግድብ ቦንድ ለመግዛት ቃል እንደገቡ ተነግሯል።
የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብሩን የታደሙት ሀገር ወዳዶቹ የዳያስፖራ አባላት ከቦንድ ግዢው በተጨማሪ በሰሜን ሸዋ አከባቢ በፀጥታ ችግር ምክንያት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የ14 ሺህ 500 ዩሮ ድጋፍ ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ገልጿል።