ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን ጋዜጠኞች ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል – የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ም/ቤት

ሚያዚያ 16/2013 (ዋልታ) – ለ6ኛው ሃገራዊና ክልላዊ ምርጫ ስኬታማነት ጋዜጠኞች ሙያዊ ስነ ምግባርን በማክበር ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ።

ምክር ቤቱ በባህር ዳርና አካባቢዋ ለሚገኙ ጋዜጠኞች የምርጫ የስነ-ምግባር መመሪያዎችን በተመለከተ ስልጠና ሰጥቷል።

የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሞላልኝ መለሰ መገናኛ ብዙሃን ለምርጫ ፍትሃዊነትና ዴሞክራሲያዊነት የጎላ ሚና አላቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚካሄደው 6ኛው ሃገራዊና ክልላዊ ምርጫ ለሀገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት በመጥቀስ፤«የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኞች ሙያዊ ስነ ምግባራቸውን አክብረው ሊሰሩ የግድ ይላል» ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀውን መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጠኞች ምርጫውን ለመዘገብ የሚያስችል መመሪያ ጋዜጠኞች መመሪያውንና ኢዲቶሪያል ፖሊሲያቸውን መሰረተ ባደረገ መልኩ ያለ አድልዎ ሊዘግቡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

«ጋዜጠኛ ብሄር የለውም» ያሉት አቶ ሞላልኝ፤ ለየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሳይወግን ወገንተኝነቱን ከእውነት ጋር ብቻ ሊያደርግ እንደሚገባም ለኢዜአ አብራርተዋል።

ሙያዊ ስነ-ምግባሩን ሳያከብር በሚሰራ ጋዜጠኛና መገናኛ ብዙሃን ላይ ምርጫ ቦርድ የሚወስደው እርምጃ እንዳለ ሆኖ ምክር ቤቱ በግልግል ዳኝነት በሚቀርቡ ጉዳዮች ዙሪያ ውሳኔ ይሰጣል ነው ያሉት።