ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ፍቅርና መተሳሰብ ሊኖረን ይገባል- ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

ሚያዝያ 25/2013 (ዋልታ) – ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ በአንድ ክልል ወይም በመዲናዋ ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ ፍቅርና መተሳሰብ ሊኖር አንደሚገባ የአገር ሽማግሌዎች መድረክ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ቀደም ብለን ብዙ የቤት ስራዎችን መስራት ነበረብን ነገር ግን አሁን ይህንን ያደረግን አይመስለኝም፣ በቀረው ጊዜ ግን የሕዝቦች አንድነትና ፍቅር ለምርጫው በሰላም መጠናቀቅ አይነተኛ ሚና እንዳለው ተገንዝበን መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

አሁንም ባለችን ጥቂት ጊዜ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ማህበራዊ አንቂዎች፣ ከፖለቲካ ውጪ ያሉ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች ወጥተው ቢያንስ ይህንን ጊዜ በሰላም እንድናልፈው የዴሞክራሲ መሞከሪያ ጊዜም እንዲሆንልን ማድረግ መቻል እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

ተመራጮቹም እንደቀደመው ጊዜ ዴሞክራሲን እናመጣለን ብለው የሌላውን አገር ቀድተው ሕዝቡን ተቀበል ከማለት ወጥተው፣ የአገሪቱን ባህል ወግ ያለውን ትውፊት በሚገባ ጠብቆ የራሱ የሆነ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ እንዲገነባ ማድረግ እንዳለባቸው መጠቆማቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡

በዚህች በቀሪዋ የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ባለፉት ጊዜያት በመሰል ችግሮች ያፈሰስነው ደም ብዙ በመሆኑ ከዚህ ወዲያ ደም እንዳይፈስ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፣ እኛ ከኢትዮጵያዊነታችንም በላይ ሰው መሆናችንን አውቀን ሰው ደግሞ ክቡር መሆኑን ተረድተን ወደልባችን መመለስ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡