ኢትዮጵያን በቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ ለማድረግ እየተሠራ ነው – ቱሪዝም ኢትዮጵያ

አቶ ስለሺ ግርማ

ሚያዝያ 25/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያን በቱሪዝም ዘርፍ ተመራጭ ሀገርና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራቶች በትኩረት እየተከናወኑ መሆናቸውን ቱሪዝም ኢትዮጵያ ገለጸ፡፡

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ እንደገለጹት፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ መንግስት የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ላይ ይገኛል፡፡

ገበታ ለሸገር ፕሮጀክትን ወደ ገበታ ለአገር በማሳደግ በአማራ ክልል ጎርጎራ፣ በኦሮሚያ ወንጪና በደቡብ ኮይሻ ሀይቆችን ጠንካራ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡

ገበታ ለሸገርን ወደ ገበታ ለአገር እንዳሳደግነው ሁሉ ገበታ ለአገርን ወደ ገበታ ለአህጉር በማሳደግ ኢትዮጵያ ሀብቷን በመጠቀም፣ እስከ አፍሪካ ገበያ አስፋፍታ ማሳየት የምትችል መሆኗን እናስመሰክራለን ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ሀገሪቱን በአፍሪካ ተምሳሌት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ቱሪስቶች ኢትዮጵያን እንዲመርጡ የሚያስችላቸው ዝግጅቶች እየተካሄዱ፣ ሥልጠናዎችም እየተሰጡ እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ ስለሺ፣ የማስተዋወቅ ስራን የሚያዘምኑ ሥራዎች መሰራታቸውንና ትግበራዎቹ በዓለም አቀፍ የቱሪዝም ገበያ ኢትዮጵያን ተወዳዳሪ ለማድረግ እንደሚያስችሉ አመልክተዋል፡፡

በመንግሥት በተለይም በፌዴራል የቱሪዝም ተቋም በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

አስጎብኚዎች ፍቃድ እንዲያገኙ፣ የግለሰብ አስጎበኚዎች ወደ አስጎብኚ ማህበራትና ተቋማት እንዲያድጉ እየተደረገ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ምደባ ስልጠና፣ የቱሪስት መዳረሻ ልማቶች፣ የገበያና ማስተዋወቅ አንዲሁም የቁጥጥርና የክትትል ሥራዎች በመከናወን ላይ እንደሆኑ መግለፃቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡