ምርጫው ያለምንም የፀጥታ ችግር በሠላም መጠናቀቁን የሲዳማ ክልል ሠላም እና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ

ሰኔ 16/2013 (ዋልታ) – ያለምንም የፀጥታ ችግር ምርጫው በሠላም መጠናቀቁን እና ህዝቡም ወደ መደበኛ የስራ እንቅስቃሴው መመለሱን የሲዳማ ክልል ሠላም እና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ሠላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በሲዳማ ክልል 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ውጤት እየተለጠፈ መሆኑን ገልጸው፣ በሁለቱም ቀናት የምርጫ ሂደቶች ምንም ችግር ሳያጋጥም መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ህዝቡም እየተለጠፈ ያለውን ውጤት ተመልክቶ በፀጋ በመቀበል ወደ መደበኛው ተግባሩ እየተመለሰ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፣ ህዝቡ በምርጫው ወቅት ለሠላሙ ዘብ በመቆም ያሳየውን ትጋት እና ጥንካሬ በቀጣይ የልማት ሥራዎችም ሊደግመው እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዋልታ በሐዋሳ ከተማ ህዝቡ ወደ መደበኛ ስራው መመለሱን ባደረገው ቅኝት የተመለከተ ሲሆን፣ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎችም ውጤቱን በፀጋ በመቀበል ለሀገር ሠላም በተባበረ ክንድ እንቆማለን ሲሉ አመላክተዋል።
(በድልአብ ለማ)