ምርጫ ቦርድ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የትብብር ጥያቄ አቀረበ

ሰኔ 12/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በተሳለጠ መልኩ እንዲካሄድ በመንግሥት ስር የሚገኙ ተቋማት ቦርዱ ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎች የተፋጠነ ምላሽ እንዲሰጡ መመሪያ እንዲያስተላልፉለት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የትብብር ጥያቄ አቅርቧል።

ቦርዱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፈው ደብዳቤ፣ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሊከናወን ጥቂት ቀናት ብቻ እንደቀሩት ገልጾ፣ “የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ከፍተኛ የትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ አቅምን የሚጠይቅ በመሆኑ በተለያዩ ሁኔታዎች ጥቂት ቦታዎች ላይ ሳንካዎች ቢገጥሙ በፍጥነት ምላሽ መስጠት እንዲቻል መንግሥትዎ በሚያዝበት በማንኛውም ተቋም ስር የሚገኝ የትራንስፖርት እና የሎጂስቲክስ አቅም እንዲሁም የምርጫውን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ የሚያስፈልግ ተጠባባቂ የሕግ አስፈፃሚ ኃይል ለምርጫው ቅድሚያ በመስጠት ፍጥነትን በተላበሰ ሁኔታ ለቦርዱ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጥ አስፈላጊውን መመሪያ እንዲያስተላልፉ” ሲል ጠይቋል።

ቦርዱ በተለያዩ የመንግሥት አካላት እስካሁን ለተደረገለት ትብብርም ምስጋናውን አቅርቧል።

መረጃውን ያገኘነው ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው፡፡