የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የምርጫ ታዛቢዎቹን ከነገ ጀምሮ እንደሚያሰማራ ተገለጸ

የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል

ሰኔ 12/2013 (ዋልታ) – የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል የምርጫ ታዛቢዎቹን ከነገ ጀምሮ እንደሚያሰማራ ተገለጸ፡፡

ሰኞ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም ለሚካሄደው 6ኛው የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርጫ የዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች ቡድን አካል የሆነው የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ታዛቢዎቹን እንደሚያሰማራ አስታውቋል።

የምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ኃይል ታዛቢ ቡድን ከ10 አባል አገራት የተውጣጣና 30 አባላት ያሉት ነው፡፡

ብሩንዲ፣ ኮሞሮስ፣ ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ሲሽየልስ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና ዩጋንዳ የተጠንቀቅ ኃይሉ አባል ሀገራት ሲሆኑ፣ ሱዳን ታዛቢ ቡድኗን እንደማትልክ በማሳወቋ የታዛቢ አባላት ቁጥር 28 እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ታዛቢ ቡድኑ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ አፋር፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሮች ምርጫውን እንደሚታዘብ ነው የተገለፀው።

(በሳሙኤል ሀጎስ)