ምክር ቤቱ ህወሓት ከሽብርተኛ ድርጅት እንዲሠረዝ ውሳኔ አሳለፈ

መጋቢት 13/2015 (ዋልታ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከሽብርተኛ ድርጅት እንዲሠረዝ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

ምክር ቤቱ ዛሬ ባሄደው ልዩ ስብሰባ ህወሓትን ከሽብርተኛ መዝገብ ለማንሳት በቀረበለት የውሳኔ ሀሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ በአብላጫ ድምፅ ውሳኔውን አፅድቋል።

ለሰሜኑ ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄ ለመስጠት በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል።

የሀገሪቱን ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት ባከበረና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሰረት በፌደራል መንግስት እና በህወሓት በኩል ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል መሰረታዊ አገለግሎቶች እንዲጀመሩ እና የሰብዓዊ እርዳታ በተሳለጠ መልኩ እንዲቀርብ ማድረጉ የሚታወቅ ነው።

በሳሙኤል ሓጎስ