ምክር ቤቱ ለመውሊድ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ

ጥቅምት 7/2014 (ዋልታ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1ሺሕ 496ኛው የነብዩ መሐመድ ልደት (መውሊድ) በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ፡፡

ምክር ቤቱ ለዋልታ በላከው መግለጫ ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የነብዩን መንገድና አስተምህሮ በመከተል ያጡና የተቸገሩ ወጎኖችን በመደገፍና በማገዝ ሊሆን ይገባል ብሏል።

ሕዝበ ሙስሊሙ ለአንድነቱና ሉኣላዊነቱ እያሳየ ያለው ቁርጠኝነት እና እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

“ባለንበት በአዲስ ምዕራፍ እንደ አባቶቻችን ሁሉ የራሳችንን ደማቅ ታሪክ ልንፅፍ ይገባል” ያለው የምክር ቤቱ መግለጫ “ይህ የሚሆነውም ጀግኖች አባቶቻችን በደምና በአጥንታቸው በከፈሉት መስዋዕትነት አንድነቷነና ሉኣላዊነቷን አስጠብቀው ያስረከቡንን አገር እኛም እንደነሱ ወቅቱ የሚጠይቀው አስፈላጊውን ትግል በማድረግና መስዋዕትነት በክፈል ታፍራና ተከብራ የቆየች ኢትዮጵያን ማስቀጠል ስንችል ነው” ሲል አብራርቷል።

ኢትዮጵያ የበለፀገችና እውነተኛ ዴሞክራሲ የሚተገበርባት እንድትሆን ሁሉም በያለበት መስክ የበኩሉን እንዲወጣም ምክር ቤቱ መልዕክት አስተላልፏል።