ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መርምሮ ውሳኔ ያሳልፋል

ነሐሴ 8/2015 (አዲስ ዋልታ) የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርምሮ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡

ከሰሞኑ በአማራ ክልል ያጋጠመውን የፀጥታ መደፍረስ ተከትሎ የፌዴራል መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 93 ንዑስ አንቀፅ 1 (ሀ) መሰረት ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 መደንገጉ ይታወሳል፡፡

በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 58 (4) እና በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 አንቀፅ 15 (1) ምክር ቤቱ በዕረፍት ላይ እያለ የምክር ቤቱን ውሳኔ የሚሹ አስቸኳይ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባ ሊጠራ እንደሚችል በተደነገገው መሠረት ለምክር ቤቱ አማካሪ ኮሚቴ አጀንዳው ቀርቦ በሙሉ ድምፅ የፀደቀ ሲሆን ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት ከቀኑ 8፡00 ሰዓት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል፡፡

በመሆኑም የምክር ቤት አባላት በዕለቱ ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በአካል በመገኘት ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ የተላለፈ ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ምክር ቤቱ መርምሮ ውሳኔ እንደሚያሳልፍም የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡