ህርዳር ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ በመመለሷ መደበኛ አገልግሎቶች መሰጠት ጀምረዋል

ነሐሴ 7/2015 (አዲስ ዋልታ) ባህርዳር ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ በመመለሷ መደበኛ አገልግሎቶች መሰጠት ጀምረዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በባህርዳር ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት ሠላም የማስከበር ስራ እያከናወነ ሲሆን ከተማዋ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴዋ ተመልሳለች፤ መደበኛ አገልግሎቶችም መሰጠት ጀምረዋል።

ሰራዊቱ ህዝቡን በማረጋጋትና ሰላምና ጸጥታን በመጠበቅ አለኝታነቱንና የህዝብ ወገንተኝነቱን በማሳየት የዜጎችን ደህንነት እየጠበቀ ይገኛል።

በከተማዋ የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴ በመደበኛነት እየተከናወነ መሆኑንና በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን ማስተዋል ተችሏል።

የከተማዋ ነዋሪዎችም በየቤተ ዕምነታቸው የአምልኮ ስርአታቸውን ፈጽመው በሰላም ወደየመጡበት ሲመለሱ መመልከት ተችሏል።

ከተማዋ ወደ ሰላማዊ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ በመግባቷ ጸጥታዋም እየተጠናከረ መጥቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ያስቀመጣቸው ትዕዛዞችና ክልከላዎች እየተተገበሩ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ህግን፣ ስርዓትንና ሞራልን መሰረት በማድረግ በዘራፊው ቡድን ላይ በወሰደው ርምጃ በአማራ ክልል ዋና ዋና ከተሞችና አካባቢዎች ወደ ሰላማዊ ሁኔታ መመለሳቸውን የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ መግለጹም ይታወሳል።

በዚህም በባሕር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ላሊበላ፣ ጎንደርና ሸዋሮቢት አካባቢ የህዝቡን ሠላም በማወክ የተሰባሰበው ዘራፊ ቡድን ላይ አስፈላጊውን ርምጃ በመውሰድ ከተሞቹን ማረጋጋት መቻሉን ገልጿል።

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምርያ ዕዝ የክልሉን ሰላም በአጭር ጊዜ ወደነበረበት ለመመለስ የመጀመሪያ ምዕራፍ ስራውን በስኬት ማጠናቀቁንና የሁለተኛ ምዕራፍ ስራዎቹን እየተገበረ መሆኑንም እንዲሁ።

የሚያከናውናቸውን ተግባራትና የሚገኙ ውጤቶችን በቀጣይ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግና ህብረተሰቡ የህግ አስካባሪ አካላት ተልዕኳቸውን በስኬት እንዲወጡ ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።