ምክር ቤቱ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችንና የብድር ስምምነቶችን መርምሮ አጸደቀ

ኅዳር 15/2015 (ዋልታ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 6ኛ መደበኛ ስብሰባ የተለያዩ ረቂቅ አዋጆችንና የብድር ስምምነቶችን መርምሮ አጽድቋል፡፡

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው የኢትዮጵያ መንግስት ከጣሊያን ሪፐብሊክ መንግስት እንዲሁም ከዓለም አቀፉ የልማት ማህበር ጋር የተደረገውን የብድር ስምምነቶች በሚመለከት በቀረበው ረቂቅ ላይ መክሯል።

የብድር ስምምነቶቹ የሀገራችንን የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ በመቅረፍ ምርታማነትን ለማሻሻል እንዲሁም በጤናው ዘርፍ የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ለሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ እንደሚውሉ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጄ አስረድተዋል፡፡

የተገኙት ብድሮች ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ ቀጣይነት ያለው ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ የምክር ቤቱ አባላት ሃሳባቸውን አንጸባርቀዋል፡፡

ምክር ቤቱ ከፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ አዋጆቹን አጽድቋል፡፡

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን እንደገና ለማቋቋም የቀረቡለትን ሁለት ረቂቅ አዋጆች መርምሮ በአብላጫ ድምፅ ማጽደቁን የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW