ምክር ቤቱ “ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” 12ኛው የኢትዮጵያ ክልል እንዲሆን ወሰነ

ሰኔ 28/2015 (ዋልታ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” 12ኛው የኢትዮጵያ ክልል እንዲሆን ውሳኔ አሳለፈ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፤ “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” የሚል ስያሜ የተሰጠውን ክልል ለመመስረት የማንነት፣ የአስተዳደር ወሰንና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ የሕዝበ ውሳኔውን አጠቃላይ ሂደት ሪፖርት ለምክር ቤቱ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በዚህም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል ስድስት ዞኖች (በጋሞ፣ በጎፋ፣ በወላይታ፣ በጌዴኦ፣ በኮንሶና በደቡብ ኦሞ) እንዲሁም አምስት ልዩ ወረዳዎች (በቡርጂ፣ በአማሮ፣ በደራሼ፣ በባስኬቶ እና በአሌ) በጋራ “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” የሚመሰርቱ ይሆናል።