ርዕሰ መስተዳድሩ በእሳት አደጋ የተቃጠለው የገበያ ማዕከል ዳግም እስከሚገነባ በጊዜያዊነት የገበያ ማዕከል እንደሚቋቋም ገለጹ

ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ

ሐምሌ 2/2015 (ዋልታ) በእሳት አደጋ የተቃጠለው የገበያ ማዕከል ዳግም እስከሚገነባ በጊዜያዊነት የገበያ ማዕከል እንደሚቋቋም የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ገለጹ፡፡

ርእሰ መስተዳድሩ በጅግጅጋ ከተማ የገበያ ማዕከል የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ አስመልክቶ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች በሚደረጉ ድጋፍና ቀጣይ ስራዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም በእሳት አደጋው ሀብት ንብረታቸው ለወደመባቸው መፅናናትን ተመኝተው እሳቱን ለማጥፋት ርብርብ እያደረጉ ጉዳት ለደረሰባቸው የክልሉ የጸጥታና የእሳት አደጋ ተከላካይ አባላት ከጉዳቱ እንዲያገግሙ ተመኝተዋል፡፡

በተጨማሪም እሳቱን ለማጥፋት ድጋፍ ላደረጉ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በሌላ በኩል በክልሉ ርእሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት የሚመራና የወደመውን የሀብት መጠን፣ እያንዳንዱ ዜጋ የወደመበት የንብረት መጠን የሚያጣራ እና ግልጽ የሆነ ምርመራና ምዝገባ የሚያደረግ ግብር ጋይል መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡

ኮሚቴው በአዲስአበባ፣ በጅግጅጋና በሌሎች የሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የድጋፍ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ ያከናውናልም ብለዋል።

በእሳት አደጋው የተቃጠለው የገበያ ማዕከል ዳግም እስከሚገነባ ድረስ በቀጣይ ሳምንታት አቅም ያላቸውና ትንሽ የንግድ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚችሉ ዜጎች በጊዜያዊነት የሚሰሩበት የገበያ ማዕከል ግብር ኃይሉ እንደሚያቋቁም ተናግረዋል።

ኮሚቴው በእሳት ቃጠሎው የወደመውን ሀብት ካጣራ በኋላ መንግሥት ጉዳት ለደረሰባቸው ነጋዴዎች የሚያደርግው ድጋፍ ይፋ እንደሚደረግ ገልጸው መሰል አደጋ ዳግም እንዳይከሰትም ዘመናዊ የገበያ ማዕከል እንዲገነባ ማብራራታቸውን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።