ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቤጂንግ የተገነባውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መርቀው ከፈቱ

ግንቦት 17/2015 (ዋልታ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የኢፌዴሪ መንግስት በቻይና ቤጂንግ ያስገነባውን አዲስ ኤምባሲና የመኖሪያ ህንጻ በዛሬው ዕለት መርቀው ከፈቱ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የቻይና የምክር ቤት አባልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ ህንጻውን መርቀው መክፈታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የኤምባሲው አዲስ ገጽታ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የአጋርነት ጠቀሜታ የበለጠ ለማጠናከር የተወሰደ እርምጃ ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያና የቻይና የቀደመ ግንኙኑት በሁለቱ አገራት መካከል ላለው ጥልቅ የሆነ ኢኮኖሚያዊ፣ በባህላዊ እና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር መሠረት የጣለ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ለቻይና-አፍሪካ ትብብር ስኬት ተምሳሌት ለመሆን ተግታ ትሰራለች ብለዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት በሁለትዮሽ፣ በክልላዊና በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ በጋራ እንደሚቆሙ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋን አዲሱ ኤምባሲ መገንባቱ የኢትዮጵያ እና የቻይና ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው የኤምባሲው ህንጻ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ቻይና ላደረገላቸው ያላሰለሰ ትብብር አመስግነው አጅግ በረቀቀ መልኩ የተገነቡት የኤምባሲው እና የመኖሪያ ቤቱ ህንጻዎች ለትውልድ የሚተርፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በቻይና የኢፌዲሪ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ባደረጉት ንግግር የኤምባሲው ግንባታ የኢትዮጵያና ቻይና ወዳጅነት ሃውልት ነው ብለዋል፡፡