ም/ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

ግንቦት 17/2015 (ዋልታ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከቻይና የመንግስት ምክር ቤት አባል እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋን ጋር ተወያይተዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይታቸው ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን ሁለትዮች ግንኙነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እና ንግድ ላይ ቻይና ትልቅ ሚና እየተጫወተች መሆኗን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቻይና ህዝብ እና መንግስት ለአፍሪካ ቀንድ አገራት እና ለአፍሪካ እንደ አጠቃላይ ታማኝ ወዳጅ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

የቻይናው አቻቸው በበኩላቸው ኢትዮጵያ ታማኝ ወዳጅ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው የቻይና መንግስት አዳዲስ ለውጦች በጋራ ለማስመዝገብ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች በሚደረጉ የመልሶ ግንባታ እና የማቋቋም ስራዎች ላይ ሀገራቸው አስተዋፅኦ እንደምታደርግ መጠቆማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግብዣ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት በትናንትናው ዕለት ቤጂንግ መግባታቸው ይታወሳል።