በአፍሪካ ህዝብ አቅም አፍሪካን በመለወጥ ልንቀይርበት ይገባል – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ግንቦት 17/2015 (ዋልታ) በአፍሪካ ህዝብ አቅም አፍሪካን በመለወጥ ልንቀይርበት ይገባል ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአፍሪካ ህብረት) የተመሰረተበትን 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ እየተከበረ በሚገኘው የአፍሪካ ቀን ላይ ነው፡፡

በዓለም ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ካላቸው አኅጉራት አፍሪካ ሁለተኛ ደረጃ ትይዛለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የሰው አቅም ለአኅጉሪቱ ብልጽግና መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።

ሙስና እና የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት የአፍሪካን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ በግብርናው መስክ ምሳሌ የሆኑ ስራዎችን እየሰራች ሰለመሆኑ አንስተዋል።

አፍሪካን ወደ ሚፈለገው ብልጽግና ለማሸጋገር አንድነትና ነጻነት ያስፈልጋል ሲሉም አክለዋል።

ህብረቱ ምስረታውን ሲያከብር በጸጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ የማግኘት ጉዳይ ሊታይ የሚገባ እንደሆነም ተናግረዋል።

በመስከረም ቸርነት