“ሩሲያ ስደርስ እንደ ትልቅ ደራሲ በደማቅ አቀባበል ነበር የተቀበሉኝ” – አያልነህ ሙላቱ

ጸኃፌ ተውኔትና ገጣሚ አያልነህ ሙላት

በሀገራችን የቴአትር ታሪክ ውስጥ ስማቸውን በደማቅ ከፃፉት ከያንያን መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ ፀሐፊ ተውኔትና ባለቅኔ አያልነህ ሙላቱ ወይም በወዳጆቹና አድናቂዎቹ አጠራር “ጋሼ” …..

ጋሼ፤ በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክና የሥነ ጹሑፍ ሥራዎች ውስጥ ከትርጉም ሥራዎች አንስቶ እስከ ወጥ የፈጠራ ሥራዎች በርካታ ትሩፋቶችን አበርክተዋል፡፡

አያልነህ ሙላት ከአዲስ ዋልታ ልዩ ቅዳሜ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ ወደ ጥበብ የገቡበትን አጋጣሚ አስታውሰዋል፡፡ ፊደል ያልቆጠሩት አርበኛ አባታቸው በሄዱበት አካባቢ ሁሉ በርካታ መጽሐፍትን ሰብስበው ይዘው ይመጡ ነበር፡፡ በኋላም እነዚህን መጽሐፍት በቤታቸው ቡና ሲፈላ እኔ እንዳነብ ይደረግ ነበር ይላሉ፡፡ በዚህ የተጀመረው ከጥበብ የመተዋወቅ አጋጣሚም ግጥም እስከ መጸፍ ደርሶ ነበር፡፡ የጻፉት ግጥምም በትምህርት ቤት አንደኛ ይወጣ የነበረ ሲሆን ጠዋት ጠዋት በሰንደቅ ዓላማ ዝግጅት ላይ ያነቡም ነበር፡፡

ብዕረኛው ጋሼ አያልነህ ተወዳጅ የሆኑላቸውን በርካታ ቴአትሮች ለህዝብ አበርክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የደራሲያን ማኃበር አማካኝነት የውጪ የትምህርት ዕድል ተመቻችቶላቸውም ወደ ሩሲያ ሄደው ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡

ሩሲያ ሲደርሱ የነበረውን አቀባበል ሲያስታውሱ “እንደ ትልቅ ገጣሚ እና እንደ ትልቅ ደራሲ አደርገው በጣም በልዩ ሁኔታ ነበር የተቀበሉኝ” ይላሉ፡፡ እዛው ሩሲያ እያሉም ከአንድ የቋንቋ አስተማሪያቸው ጋር የነበራቸው አስቂኝ አጋጣሚንም ያወሳሉ፡፡

አስተማሪዋ ተከታታይ ጥያቄ እሳቸውን ብቻ ትጠይቃለች በነገሩ ግራ የተጋቡት አያልነህ ሙላትም ጓደኞቻቸውን ሲጠይቁ “ወዳህ ሊሆን ይችላል” በማለት በሩሲያ ባህል መሰረት እንዲገናኙ ያደርጓቸዋል፡፡ በሩሲያ ባህል መሰረት ደግሞ ከሴት ጋር ቀጠሮ ያለው ሰው አበባ ይዞ መሄድ ያስፈልገዋል፡፡ አበባውም በእጅ መያዝ ያለበት ሲሆን ምንም ነገር ውስጥ መግባት የለበትም፡፡

ይህን ያለመዱት አያልነህ ሙላት ግን አበባውን ገዝተው ከክረምት ካፖርታቸው ኪስ ውስጥ ወሽቀው ይሄዳሉ፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን መጀመሪያ ላይ አበባውን መስጠትም ረስተውት ኖሮ መጨረሻ ላይ አስታውሰው ሊሰጧት ሲሉ ቅጠሎቹ ረግፈዋል፡፡ መምህሯም ሞራሌን ለመጠበቅ ብላ ይሁን አላውቅም ከረገፈው ቅጠል ጋር አብራ ተቀብላኝ ነበር ሲሉ በፈገግታ አስታውሰዋል፡፡

ይህ በተፈጠረ በነጋታው በጋዜጣ ላይ ግን The conflict of culture (የባህሎች ግጭት) የሚል ፀሑፍ መፃፏን ገልፀዋል፡፡

ጋሼ የአለማየሁ እሸቴን…..
እኔ ልኮራመት እኔ ከሰል ልምሰል
ስቀሽ አታስቂኝ የደላሽ መስል… የሚለውን ሙዚቃ አብዝተው እንደሚወዱትም ነግረውናል፡፡

ፀሐፊ ተውኔትና ባለቅኔ አያልነህ ሙላቱ ከዩኒቨርሲቲ መምህርነት እስከ ባህል ማዕከል ዳይሬክተርነት ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡