ሕጋዊ የሴት አመራሮች ማኅበር ማቋቋም የቀጣይ ትኩረት ሊሆን ይገባል – ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ

መጋቢት 23/2016 (አዲስ ዋልታ) ሕጋዊ የሴት አመራሮች ማኅበርና በየጊዜው ስለ ሴቶች መሪነት ውይይት የሚያደርግ ሃሳብ አመንጪ ቡድን ማቋቋም የቀጣይ ትኩረት ሊሆን ይገባል ሲሉ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ አሳሰቡ።

በፕሬዝዳንቷ አነሳሽነት ከክልሎችና የተለያዩ ክፍሎች የተውጣጡ 180 ሴት አመራሮችና 130 ሴት ፓርላማ አባላት የመሪነት ሥልጠና ተሳታፊዎች የጋራ ስብሰባ ተካሂዷል።

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ በዚህ ስብሰባ ላይ የሥልጠናው ዓላማ ወደ ከፍተኛ አመራርነት ለማደግ የሚችሉ ብቁ ሴቶችን ማፍራት፣ የሴት አመራሮች መረጃ መያዝ፣ ወደፊት እንዲመጡ ማበረታት፣ ማገዝ እንዲሁም እርስ በእርስ የሚደጋገፉበትን መንገድ መፍጠር ነው ብለዋል።

ፕሬዝዳንቷ አክለውም ተከታታይ ሥልጠና እንደሚያስፈልግና እዚህ የተገኘውን ልምድና እውቀት ታች ላሉ ሴቶች እንዲያስተላልፉ ለስብሰባው ተሳታፊዎች አሳስበዋል።

ትምህርት ገደብ አልባ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዝዳንቷ የሌሎችንም ሃሳብ አዳምጡ፣ በሴቶች መካከል ትብብር እንጂ ፉክክር አይገባም ሲሉ ምክረ ሃሳብ መለገሳቸውን ከፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።