ሐምሌ 5/2015 (ዋልታ) ሩሲያ የአፍሪካ ሀገራት ሉዓላዊነትና ነፃነት ላይ የተመሰረተው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትፈልጋለች ሲሉ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ተርኪሂን ገለጹ።
በአሮፓዊያኑ ከሐምሌ 27 እስከ 28 በሴንት ፒተርስበርግ ከሚካሄደው ሁለተኛው የሩሲያ አፍሪካ ጉበኤ ቀደም ብሎ እየተካሄደ በሚገኘው ፎረም ላይ ምልዕክታቸውን ያስተላለፉት አምባሳደሩ ሩሲያ የአፍሪካም ሆነ የሌሎች ሀገራት ሉዓላዊነት እንዲጠበቅ እንደምትፍልግ እና ለዚህም ትኩረት ሰጥታ እንደምትሰራ አመላክተዋል፡፡
የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ምርታማነትን መጨመር፣ በኬሚካል ኢንዱስትሪ፣ የፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች፣ በኃይል ዘርፍ፣ ትምህርትና ጤና በጉባኤው ትኩረት የሚደረግባቸው እጀንዳዎች ስለመሆናቸውም ተናግረዋል።
ሩሲያ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ችግሮች የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎችንም ችግሮች በጋራ ለመፍታት ቁርጠኛ ነችም ብለዋል።
አፍሪካ የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ነፃነት ሊኖራት ይገባል ያሉት አምባሳደሩ በተለይ ከምዕራባዊያን ተፅዕኖ ለመላቀቅ በራስ ገንዘብ የምንገበያይበት የንግድ ሥርዓት እውን እንዲሆን ሀገሬ ጥረት ታደርጋለችም ነው ያሉት።
በምግብ ራስን መቻል፣ የግብርና ምርቶችና ግብዓቶች ለአፍሪካ ሀገራት ተደራሽ እንዲሆኑ ከአህጉሪቷ ጋር ያለንን ግንኙት አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም ገልጸዋል።
ሩሲያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ትኩረት ትሰጣለች፤ የሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ ደግሞ ለዚህ ምቹ መደላድል ይፈጥራል ብለን እናምናለንም ነው ያሉት።
በትዕግስት ዘላለም