ርዕሰ መስተዳድሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ሥራ አስጀመሩ

ግንቦት7/2014 (ዋልታ) የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በክልሉ ከ30 ሚሊየን ብር በሆነ ወጪ የተከናወኑ እና የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ሥራ አስጀመሩ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችንም የጎበኙ ሲሆን ፕሮጀክቶቹ በአፋጣኝ ተጠናቀው ሥራ እንዲጀምሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የክልሉ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ ዲኒ ረመዳን ፕሮጀክቶችን አስመልክተው እንደተናገሩት በክልሉ ከ30 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተከናወኑ ከነበሩ 17 ፕሮጀክቶች መካከል ሰምንቱ ተጠናቀው በእለቱ ሥራ ጀምረዋል።
ቀሪዎቹ ፕሮጀክቶችም ከ95 በመቶ በላይ ተጠናቀዋል ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ በተለይም የድሃ ድሃ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ከማድረግና ክልሉንም ፅዱ ከማድረግ አንፃር ጉልህ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ከተከናወኑ ፕሮጀክቶችም የጋራ መፀዳጃ ቤቶች፣ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች እና ሌሎች ፕሮጀክቶች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪም 409 የድሃ ድሃ እማዎራዎችንና አባዎራዎችን ተጠቃሚ ያደረገ የውሃ መሰረተ ልማት መከናወኑንም ገልፀዋል።
ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)