ርዕሰ መስተዳድሩ የስንዴ ምርታማነትን በአምስት እጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገለጹ

ግንቦት 4/2015 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የስንዴ ምርታማነትን በአምስት እጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን የገለጹት በሳይንስ ሙዚየም የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ምርምር ፈጠራዎች የተካተቱበትን የግብርና ሳይንስ ዐውደ ርዕይ በጎበኙበት ወቅት ነው።

ዐውደ ርዕዩ የተሰሩ ስራዎችን ለመገምገም የሚያስችል እና ቀጣይ ስራዎች ምን መምሰል አለባቸው የሚለውን የሚያመላክት ነውም ብለዋል።

አምራችን ከተጠቃሚው ጋር ለማገናኘት እና ግብዓቶች እና ቴክኖሎጂዋች የት እንደሚገኙ ለማሳየት የሚጠቅም በመሆኑ በሌሎችም ክልሎች እንዲህ ያለ ዐውደ ርዕዮችን ማዘጋጀት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ግብርናው በመንግስት በኩል ልዩ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ እንደ ክልል በተለይ የስንዴ ምርትን በአምስት እጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ዘንድሮ በክልሉ በክረምት እና በበጋ 100 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በማምረት በስንዴ አዲስ ታሪክ ተመዝግቧል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይ ዓመት ወደ 180 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።

ይህ እቅድ እንዲሳካም ግብርናውን በቴክኖሎጂ በመደገፍና ማዘመን እንዲሁም የመካናይዜሽን አጠቃቀምን ዓለም የደረሰበት ላይ ለማድረስ መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች በዛሬው ዕለት ዐውደ ርዕዩን ጎብኝተዋል።

በትዕግስት ዘላለም