የቡድን ሰባት አባል አገራት ፋይናንስ ሚኒስትሮች ቻይና ላይ ስለሚወስዱት እርምጃ መስማማት አልቻሉም

ግንቦት 4/2015 (ዋልታ) በኢኮኖሜ የበለጸጉ የቡድን ሰባት አገራት ፋይናንስ ሚኒስትሮች ቻይና ላይ ስለሚወስዱት እርምጃ መስማማት አለመቻላቸው ተገለጸ፡፡

በጃፓን ሊቀመንበርነት የሚመራው የሚኒስትሮቹ ስብሰባ በጃፓን ኒጋታ ከተማ ለሦስት ቀናት እየተካሄደ ሲሆን የስብሰባቸው ዋና አጀንዳ የዓለም የንግድ ሰንሰለትን አማራጭ በማብዛት ከቤጅንግ ተፅዕኖ መላቀቅ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ተብሏል፡፡

በስብሰባው በቻይና ኢንቨስትመንት ላይ የተመረጠ ቁጥጥር እና እቀባ ማድረግ ላይ ክርክር አድርገው አንድ ወጥ አቋም ላይ ለመድረስ ሳይችሉ መቅረታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

በተለይ በውጭ ንግድ ላይ የተንጠለጠለ ኢኮኖሚ ያላቸው እንደ ጃፓን እና ጀርመን ያሉ አገራት የሚወሰደው እርምጃ በራሳቸው ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ቀውስ ያመጣል በማለት የቡድኑን ጠንካራ ጸረ-ቻይና አቋም ለመደገፍ እያንገራገሩ መሆኑ ተነግሯል፡፡

በቻይና ላይ ጠንከር እና ከረር ያለ እርምጃ እንዲወሰድ ከሚፈልጉ አገራት ውስጥ አሜሪካ ዋነኛዋ ስትሆን ጠንከር ያለ እርምጃ የመውሰዱን ውሳኔ እንዲደግፉ አባል አገራትን በማግባባት ላይ መሆኗን ዘገባው አመላክቷል፡፡

የፀረ-ቻይና አጀንዳ ያሳሰባት ጃፓን ቻይና ውስጥ በሚደረግ ኢንቨስትመንት ላይ ቁጥጥር መደረጉ የዓለምን ንግድ ዕድገት እና የራሷን ኢኮኖሚ ይጎዳዋል በሚል አጀንዳውን ለመደገፍ መቸገሯን አስታውቃለች፡፡

ቻይናን ከዓለም ንግድ ሰንሰለት ለመነጠል መሞከር የዓለምን ንግድ ይከፋፍላል፤ የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገትን ይጎዳል በማለት የዘርፉ ባለሙያዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

የአገራቱ ፋይናንስ ሚኒስትሮች በነገው ዕለት የጋራ መግለጫ እንደሚያወጡም ይጠበቃል፡፡

የቡድን ሰባት አባል አገራት የሚባሉት አሜሪካ፣ ጃፓን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና ካናዳ ናቸው፡፡