ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን ዪኒሴፍ በክልሉ ለሚያደርጋቸው ድጋፎች ምሥጋና አቀረቡ

መስከረም 3/2015 (ዋልታ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የህጻናት ፈንድ (ዩኒሴፍ) በክልሉ ላደረጋቸውና እያደረጋቸው ላሉ ድጋፎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ ጃንፍራንኮ ሮቲግሊያኖ ከሚመራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በቆይታቸውም ዩኒሴፍና አጋሮቹ በክልሉ እስካሁን ያደረጋቸውን ድጋፎች እና የሚታዩ ክፍተቶችን የሚያመላክት መነሻ ሠነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በውይይቱ ላይ ድርጅቱ ላደረጋቸው ድጋፎች ምሥጋና ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድር አሻደሊ በክልሉ ተከስቶ በነበረው ግጭት የወደሙ ተቋማትን መልሶ በመገንባት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል እንዲሁም ከቀያቸው ተፈናቅለው ለቆዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ የዩኒሴፍና አጋሮቹ እገዛ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

የዩኒሴፉ ተወካይ በበኩላቸው በርዕሰ-መስተዳድሩ ስለተደረገላቸው አቀባበልና ገለፃ አመስግነው ዩኒሴፍ እያደረገ ያለውን እገዛና ድጋፍ የበለጠ አጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን በክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡