በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የ550 ሚሊየን ዶላር ፈንድ ይፋ ተደረገ

መስከረም 3/2015 (ዋልታ) ‘ሕብረት ለአፍሪካ የአረንጓዴ አብዮት’ (AGRA) የተሰኘ ድርጅት በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ የ550 ሚሊየን ዶላር ፈንድ ይፋ አድርጓል፡፡

ፈንዱ አፍሪካ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በምግብ ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ትግል ለማገዝ ይውላልም ተብሏል፡፡

በዚህ አዲስ ፖሊሲ አግራ በአህጉሪቱ 15 ሀገራት የሚገኙ ከ28 ሚሊየን በላይ አርሶ አደሮች በግብርና ስራቸው ምርታማነትን በማሳደግ ገቢያቸውን ከፍ ለማድረግ ማቀዱን የደርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ እና የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገልጸዋል፡፡

ከአውሮፓዊያኑ 2023 እስከ 2027 ባሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረገው ይህ ፕሮጀክት፤ በተሻሻለ ዘር አቅርቦት፣ መንግስት በዘር ላይ በሚያደርገው ተሳትፎ፣ በግብርና ዘርፉ የአቅርቦት ሰንሰለት እና የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ላይ ትኩረት ያደርጋልም ማለታውን ዘ ኢስት አፍሪካ አስነብቧል፡፡

በነስረዲን ኑሩ