ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር በማለፍ ሕጋዊ ያልሆነ ድርጊት እየፈጸመች መሆኑ ተገለጸ

                             አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

ሱዳን በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ እየፈጸመች ያለውን ሕጋዊ ያልሆነ ድርጊት አጠናክራ መቀጠሏን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ፡፡

የሳምንቱን የሀገሪቱ አበይት የዲፕሎማሲ ክንውኖች አስመልክተው መግለጫ የሰጡት አምባሳደር ዲና፣ ኢትዮጵያ ጦርነት ትርፍ እንደሌለው የምትረዳ እና በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ግንባር ቀደም የሆነች ሀገር ናት ብለዋል፡፡

ሱዳን በድንበር አካባቢ በተጠናከረ ሁኔታ ጦሯን እያንቀሳቀሰች ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ህግጋት የምትመራ እና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ችግሮችን የምትፈታ ሀገር መሆኗ ተገልጿል።

ሁለቱ ሃገራትን ወደ ግጭት በማስገባት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሰሩ የተለያዩ ሶስተኛ አካላት ቢኖሩም የኢትዮጵያና ሱዳን ሕዝቦች ረጅም ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው በመሆናቸው የጋራ ዕድገት እንጂ ጦርነት እንደማይፈልጉም ተጠቁሟል።

ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ ለሠላምና ዲፕሎማሲ ቅድሚያ እንደምትሰጥ ጠቁመው የሱዳን ጦር ወደ ድንበሯ ጥሶ በመግባት እያደረገ ያለውን ሕገወጥ እንቅሰቃሴ መታገሷ ከፍርሃትና ከመወላወል ጋር የተገናኘ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

እ.አ.አ በ1902 የተደረገውን ድንበር የማካለል ታሪክ ተከትሎ በተለያዩ ጊዜያት የተጀመሩ የጋራ የድንበር ማካለል ሠላማዊ እንቅስቃሴዎች በመመለስ የሁለቱን አገራት የድንበር ችግር መፍታት ተገቢ እንደሆነም ገልጸዋል።

ግብፅ እና ሱዳን ሆን ብለው የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር እንዲጓተት እያደረጉ ነው ያሉት አምባሳደሩ፣ ሁለቱ ሀገራት ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት መፍትሔ እንዳያገኝ እየሰሩ በመሆናቸው በጸጥታው ምክር ቤት እንዲታይ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡

በሳምንቱ አበይት የዲፕሎማሲ ዜጋ ተኮር ክንውኖች ከሳውዲ እና ከኦማን ወደ 742 የሚደርሱ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን አምባሳደር ዲና አስታውቀዋል፡፡

(በመስከረም ቸርነት)