ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር አልፋ በመግባት አለም አቀፍ ህግን እንደጣሰች የድንበር ኮሚሽን ገለጸ

ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር አልፋ በመግባት የአለም አቀፍ ህግ መጣሷን  የኢትዮ-ሱዳን የጋራ ድንበር ኮሚሽን ኮሚቴ አባል አምባሳደር ኢብራሂም እንድሪስ አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል የተወከሉት  የኢትዮ-ሱዳን የጋራ ድንበር  ኮሚሽን ኮሚቴ አባላት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የድንበር ኮሚሽን ኮሚቴ አባል አምባሳደር ኢብራሂም እንድሪስ የሱዳን ድርጊት የሀገራቱን የቀደመ ታሪክ የማይመጥን መሆኑን ገልጸው፣ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሱዳን ጦር ከኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በፍጥነት ለቆ ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

በዚህ ግጭት ተጎጂዎቹ ሁለቱ ሀገራት በመሆናቸው ለውጪ ጣልቃ ገብነት እድል መክፈት እንደሌለባቸውም ተጠቁሟል፡፡

እ.ኤ.አ በ1972 ሁለቱ ሀገራት በመንግስታቸው ተቀባይነት ያለው የድንበር ማካለል ስራ እስኪሰራ ድረስ ነባራዊ ሁኔታ ተከብሮ እንዲቆይ ተስማምተው እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ላይ የሁለቱ ሀገራት የጋራ የድንበር ኮሚሽን የሀገራቱን የድንበር ጉዳይ እልባት ለመስጠት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ባለበት ወቅት የሱዳን ጦር ድንበር አልፎ ኢትዮጵያ መግባቱ አለም አቀፍ ህግን መጣስ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ውዝግብ 100 አመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በአጼ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስት በሀገራቱ መካከል የተለያዩ ስምምነቶች ተደርገው እ.ኤ.አ በ1903 ጉዊን በተባለ እንግሊዛዊ ሰርቬየር የሀገራቱ የጋራ ድንበር ተከልሎ እንደነበርና ኢትዮጵያ ከእውቅናዬ ውጪ ነው በሚል ምክንያት ስላልተቀበለችው በተደጋጋሚ በሁለቱ ሀገራት መካከል የድንበር ውዝግብ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

ሀገራቱ እ.ኤ.አ በ1972 የማስተወሻ ልውውጥን በመፈራረም የጋራ ድንበራቸውን ለማካለል የተስማሙ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ሱዳን ስምምነቱን በመተው ጦሯን የኢትዮጵያን ድንበር አሳልፋ አስገብታለች፡፡

(በመስከረም ቸርነት)