ሩዋንዳ ወደ ዋና ከተማዋ በሚገቡ መንገደኞች ላይ እገዳ ጣለች

ሩዋንዳ  ከየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢና ከሌሎች አገራት ወደ ዋና ከተማዋ ኪጋሊ በሚገቡ መንገደኞች ላይ እገዳ መጣሏን በትናንትናው ዕለት አስታውቃለች፡፡

በሀገሪቱ በኮሮና ቫይረስ ምክኒያት እየደረሰ ያለው የሞት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሻቀቡንና በአጠቃላይ የቫይረሱ የስርጭት መጠን እየጨመረ በመምጣቱ እገዳው መጣሉን የሩዋንዳ ባዮሜዲካል ሴንተር (አር.ቢ.ሲ) ያወጣው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከትናንት ማክሰኞ ጥር 5 ጀምሮ ወደ ዋና ከተማዋ ኪጋሊ የሚወስዱ የህዝብና የግል ትራንስፖርት አገልሎቶች ለቀጣዮቹ 15 ቀናት እንዳይንቀሳቀሱ እገዳ መጣሉን መንግስት ይፋ አድርጓል፡፡

የሩዋንዳ ጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ትላንት ባወጣው መረጃ ወደ ዋና ከተማዋ ኪጋሊ ጉዞ ለማድረግ የሚፈቀድላቸው አካላት እንዳሉና እነሱም ለህክምና የሚጓዙና ቀጠሮ ያላቸው፣ አስፈላጊ ሸቀጦችን ወደ ከተማዋ የሚያጉጉዙ ብቻ እንደሆኑና ይህም ቢሆን በአንድ ተሸከርካሪ ላይ ከ2 ሰዎች በላይ መሳፈር እንደማይችሉ አስታውቀዋል፡፡

እስካሁን በአገሪቷ 110 ሰዎች በቫይረሱ ምክኒያት ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከግማሽ በላይ የሚሆነው ቁጥር የተመዘገበው ግን በታህሳስ ወር እንደሆነና መንግስት እየወሰደ ላለው እርምጃ ይህ ምክኒያት እንደሆነ ተነስቷል፡፡

በታህሳስ ወር ብቻ አጠቃላይ ስርጭቱ ከነበረበት 0.5 በመቶ ወደ 7.6 በመቶ ከፍ ማለቱን እና ይህ ደግሞ አሰደንጋጭ የሚባል እንደሆነም እየተገለፀ ይገኛል፡፡

መንግስት ባወጣው መግለጫ ህዝቡ ማህበራዊ እንቅስቃሴውን እንዲገድብና አሰፈላጊ የሚባሉ አገልግሎቶችን ለማግኘት ካልሆነ መሰባሰብ እንደማይቻል አስታውቋል፡፡

በመሆኑም ከትላንት ጀምሮ በሁሉም የንግድ ሱቆች ገበያዎችና የገበያ ማዕከሎች የሰአት ገደብ እንዲጣል ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም ማህበራዊ ስብሰባዎች እና ዝግጅቶች፣ ሃይማኖታዊ እና  የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች፣ ስብሰባዎች የተከለከሉ ናቸውም ተብሏል፡፡

ስርጭቱን ለመግታት ሁሉም የሀገሪቷ ዜጎች አካላዊ እርቀታቸውን እንዲጠብቁ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ እንዲጠቀሙ ፣የእጅ ንፅህናቸውን እንዲጠብቁና ከህክምና ባለሞያዎች የሚሰጡ መልእክቶችን እንዲተገብሩ መልዕክት የተላለፈ ሲሆን ይህን ተላልፎ የተገኘ ሰው ቅጣት እንሚጠብቀውም ተገለፁል፡፡

አጠቃላይ ወሳኔው በጠቅላይ ሚኒስትር ኢዶዋርድ ንግሬንት በተመራው የካቤኔ ሰብሰባ የተወሰነ እንደሆነም ታውቋል፡፡

በአለም ላይ የተነሳውን ሁለተኛውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እየተወሰደው ባለው በዚህ እርምጃ  ወደ ሩዋንዳ የሚገቡ ቱሪስቶች ላይ ምንም አይነት ገደብ አለመጣሉን እና አሰፈላጊውን ቅድመ ምርመራ እያደረጉና ማስረጃ እያመጡ ወደ ሀገሪቷ መግባት እንደሚችሉም መንግስት ገልፁል፡፡

እስከ አሁን በሩዋንዳ 8,955 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 110 ሰዎች ህይወታቸውን አተዋል ሲል የዘገበው ኢስት አፍሪካን ኒውስ ነው፡፡