ሻሸመኔ

ሻሸመኔ

#ከተሞቻችን

የምዕራብ አርሲ ዞን ዋና መቀመጫ የሆነችው የሻሸመኔ ከተማ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ አቅጣጫ 255 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን በ1913 እንደተቆረቆረች ይነገርላታል።

ከከተማዋ ስያሜ ጋር በተያያዘ እንደ አፈታሪክ የምትነሳ አንዲት “ሻሼ” የምትባል እንግዳ ተቀባይ ሴት በአካባቢው ትኖር እንደነበር እና የሻሼ ቤት ወይም በኦሮምኛ “መነ-ሻሼ” የሚለው የስፍራው ስያሜ በጊዜ ሂደት ተቀይሮ ሻሸመኔ እንደተባለ በታሪክ ይወሳል።

ወይና ደጋ የአየር ንብረት ያላት የሻሸመኔ ከተማ ከባህር ጠለል በላይ 1937 ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች።

ጀምበር የማይጠልቅባት የሻሸመኔ ከተማ የዞኑ ዋና የንግድ እና የትራንስፖርት ማዕከል ስትሆን ሐዋሳን ጨምሮ ወላይታ እና ዲላን የምታገናኝ ባለ5 በር ኮሪደር ከተማ ነች።

የተለያዩ ብሄረሰቦችን በጉያዋ ያቀፈችው ሻሸመኔ በ12 ወረዳ እና 4 ክፍለ ከተማዎች የተዋቀረች ስትሆን አቦስቶ፣ ጎፋ፣ አዋሾ፣ ኩዬራ እና አራዳ ከሰፈር ስያሜዎቹ መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

ከበሀማስ፣ ከኮቤኮ፣ ከካሪቢያን እና ከጃማይካ የመጡ ዜጎች ለበርካታ ዓመታት ከትመው የሚኖሩባት ከተማ እንደሆነችም ይነገርላታል።

በከተማዋ ሻሸመኔ ሙዚየምና የተለያዩ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ሊድ ስታር ኢንተርናሽናል አካዳሚ፣ ሉሲ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ሚሊኒየም ሻሸመኔ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ እናት ኮሌጅ እና የሻሸመኔ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ይገኙበታል።

ከከተማዋ ጥቂት ኪሎሜትሮችን ወጣ ሲባል ደግሞ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክትም አላት።

ከሻሸመኔ ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው የአቢጃታ እና ሻላ ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ የራስተፈሪያን ማህበረሰብ ፣ የሐምዛ መስጊድ እና የባናና አርት ጋለሪ በከተማዋ የሚገኙ የጉብኝት መዳረሻዎች ናቸው። ሻሸመኔ ብዙ የሀገር ባለውለታዎችንም አፍርታለች።

ፀሐይ የማይጠልቅባት ከተማ እየተባለች በምትጠራው ሻሸመኔ ከተማ ተወልዳችሁ ያደጋችሁም ሆነ በተለያየ አጋጣሚ ያያችኋትና ልዩ ትዝታን ያተረፋችሁ ትዝታችሁን አጋሩን።
መልካም ሳምንት!!

በአዲስዓለም ግደይ