ሹዋሊድ በዩኔስኮ መመዝገቡ ሀረርን የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን አድርጓታል – ኦርዲን በድሪ

የሹዋሊድ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ የባህል ዐውደ ርዕይ እና ፌስቲቫል በሐረር ከተማ ሲከፈት

ሚያዚያ 8/2016 (አዲስ ዋልታ) የሹዋሊድ ክብረ በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ ሀረርን የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን እና በሀገር አቀፍ ደረጃ በቱሪዝሙ ዘርፍ የራሷን ሚና እንድትጫወት ማድረጓን የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ፡፡

የሹዋሊድ ክብረ በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ በማይዳሰስ ቅርስነት በዩኔስኮ መመዝገቡ ለሀገር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህም ሀረር ከተማ ሁለት ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስመዝገብ የቻለች መሆኗን ገልጸዋል፡፡

የኢፌዴሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው ሀረር የብዙ ታሪኮች መነሻ የሆነች ጥንታዊት ከተማ መሆኗን አንስተው ሹዋሊድ ከተማዋን የሚያስተዋውቅ የፍቅር ክብረ በዓል ነው ብለዋል፡፡

እንደ ሹዋሊድ ዓይነት ሀብቶቻችንን አስጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ከመንግስት ጋር በትብብር መስራት ይኖርበታል ሲሉም ገልጸዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ናሲሴ ጫሊ ሀረር ከተማ በውስጧ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ቅርሶች አምቃ የያዘች ሙዚየም ናት ብለዋል፡፡

የሸዋሊድ በዓል አከባበር በሀረር

ሀገሪቱ የበርካታ የቱሪዝም ሀብቶች ባለቤት እንደመሆኗ በሚፈለገው ልክ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ሀገሪቱ መጠቀም የምትችልበትን መንገድ ለማፈላለግ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነም አንስተዋል፡፡

ሀገሪቱን ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ መንግስት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ሀብት በመሆናቸው መንከባከብ እና መጠበቅ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የሹዋሊድ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ የባህል ዐውደ ርዕይ እና ፌስቲቫል በዛሬው ዕለት የተለያዩ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በሀረር ከተማ ተከፍቷል።

የሹዋሊድ ክብረ በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት በያዝነው ዓመት መመዝገቡ ይታወቃል፡፡

ብርሃኑ አበራ (ከሀረር)