ቅዱስ ሲኖዶስ ሀገራዊ ሰላም በተመለከተ ተወያይቶ ውሳኔ በማስተላለፍ ውሳኔውን የሚያስፈጽሙ አባቶችን ሰየመ

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ

ግንቦት 11/2014 (ዋልታ) የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሀገራዊ ሰላም በተመለከተ ተወያይቶ ውሳኔ በማስተላለፍ ውሳኔውን የሚያስፈጽሙ አባቶችን ሰይሟል።

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ 23 የመወያያ አጀንዳዎችን አጽድቆ በመወያየት ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን ማስተላለፍ ጀምሯል።

ዓመታዊው የግንቦቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ርክበ ካህናት ጉባኤ ግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ.ም በጸሎት ከተጀመረ በኋላ በትላንትናው ዕለት በጠዋቱ መርኃ ግብር የቅዱስነታቸውን የመክፈቻ መልዕክት አዳምጧል።

በመቀጠልም ሰባት አባቶችን የያዘ የአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ አባላትን በመሰየም አጀንዳዎችን አዘጋጅተው እንዲያቀርቡ ካደረገ በኋላ በኮሚቴው ተዘጋጅተው የቀረቡለትን አጀንዳዎች መርምሮ ማስተካከያ ካደረገባቸው በኋላ አጽድቋቸዋል።

በመቀጠልም በአጀንዳዎቹ ቅደም ተከተል መሰረት የቅዱስነታቸውን የመክፈቻ መልዕክት ያጸደቀ ሲሆን ሀገራዊ ሰላም በተመለከተ ተወያይቶ ውሳኔ በማስተላለፍ ውሳኔውን የሚያስፈጽሙ አባቶችን መሰየሙ ተገልጿል።

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬ ጠዋት የጉባኤ ውሎው ልዩ ልዩ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፍ የሚጠበቅ ሲሆን ከሰዓት በኋላን ጨምሮ እስከ እሁድ ድረስ በበዓላት ምክንያት ጉባኤው እንደማይካሄድ ታውቋል።

ምልዐተ ጉባኤው ከሰኞ ጠዋት ጀምሮ መደበኛ ስብሰባውን በማከናወን ቀሪ አጀንዳዎችን መሰረት ያደረጉ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የቤተክርቲያኒቱ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ መረጃ ያመለክታል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW