ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሱዳኑ አል-ሂላል ጋር ዛሬ ይጫወታል

መስከረም 1/2015 (ዋልታ) ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በየአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ-ማጣሪያ ከሱዳኑ አል-ሂላል ጋር ዛሬ ይጫወታል።
የ2022/23 የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊጉ የማጣሪያ ጨዋታዎች በያዝነው ሳምንት ተጀምረዋል።
ኢትዮጵያን ወክሎ በውድድሩ ላይ የሚሳተፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ ከቀኑ 10 ሰአት በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከሱዳኑ አል-ሂላል ጋር የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን ያካሂዳል።
የ15 ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር የተመለሰው ከአራት ዓመት በኋላ ነው።
ክለቡ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ሲሳተፍ የዘንድሮው ለ14ኛ ጊዜ ነው።
ፈረሰኞቹ ለመጨረሻ ጊዜ በሻምፒዮንስ ሊጉ የተሳተፉት እ.አ.አ በ2017/18 የውድድር ዓመት ሲሆን በወቅቱ 16 ውስጥ በመግባት ትልቁን ውጤታቻውን አስመዝግበዋል።
በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመራው ቡድን ለጨዋታው ለአንድ ወር የሚሆን ጊዜ ቢሾፍቱ በሚገኘው የይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ልምምዱን ሲያደርግ ቆይቷል።
ፈረሰኞቹ በአካዳሚው ከሱዳኑ አል ሜሪክ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አድርገው 3 ለ 1 አሸንፈዋል።
ከሱዳኑ ክለብ ጋር ሁለተኛ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ ቢያዝም በአካዳሚው በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 40ኛው ደቂቃ ላይ መቋረጡ የሚታወስ ነው።
ፈረሰኞቹ የታንዛንያው ሲምባ ክለብ 86ኛ ዓመት ምስረታ በማስመልከት በቤንጃሚን ምካፓ ስታዲየም ከክለቡ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አድርገው 2 ለ 0 መሸነፋቸው አይዘነጋም።
የፈረሰኞቹ ተጋጣሚ አል-ሂላል የዘንድሮ የሱዳን ፕሪሚየር አሸናፊ ሲሆን የሊጉን ዋንጫ ለ29ኝ ጊዜ በማንሳት የበላይነቱን ይዟል።
ክለቡ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ሁለት ጊዜ ለፍጻሜ መድረስ የቻለ ነው።
23 ተጫዋቾችን የያዘው የፍሎረንት ኢቢንጌ ስብስብ ለዛሬው ጨዋታ የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት ጨዋታው በሚካሄድበት ባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም አድርጓል።
ሁለቱ ክለቦች የመልስ ጨዋታቸውን መስከረም 8 ቀን 2014 ዓ.ም በአል-ሂላል ስታዲየም ያደርጋሉ።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚውን በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ በቀጣዩ ዙር ከታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስና ከደቡብ ሱዳኑ ዛላን ኤፍሲ ሩምቤክ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።