በሀረሪ ክልል የተለያዩ የእምነት አባቶች እና ተከታዮች የኢድ አልፈጥር በዓል ማክበሪያ ስፍራ አፀዱ

ሚያዝያ 12/2015 (ዋልታ) በሀረሪ ክልል የሚገኙ የተለያዩ የእምነት አባቶች እና ተከታዮች ነገ የሚከበረውን 1 ሺሕ 444ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ የበዓሉ ማክበሪያ ስፍራን አፀዱ።

በጽዳት መርኃ ግብሩ ላይ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ እምነት ተከታዮችና የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በፅዳት መርኃ ግብሩ ላይ የተሳተፉ የእምነት አባቶች የእስልምና እምነት ተከታዮች በነገው እለት ለሚከበረው የኢድ አል ዓድሃ በዓል ማክበሪያ ስፍራን ማፅዳታቸውን ጠቁመው ይህም በሃይማኖቶች መካከል መቻቻልን፣ አብሮነትንና ሰላምን ያጎለብታል ብለዋል።

የሁሉም ሃይማኖቶች አስተምሮት በጋራ መኖርንና መደጋገፍን የሚያስተምር በመሆኑ መሰል ተግባራት መጠናከር እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

በጽዳት መርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን ዋደራ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ እምነት ተከታዮች በየበዓላቱ ተሰባስበው ማፅዳታቸው የክልሉን ሰላም የበለጠ ያጠናክራል ብለዋል።

በዓሉ በሰላም እንዲከናወን አስፈላጊ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው የክልሉ ህዝብ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ እና የክልሉ ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር ቅርንጫፍ)