የሱዳን ተዋጊ ኃይሎች የ24 ሰዓት የተኩስ አቁም ስምምነት አወጁ

ሚያዝያ 10/2015 (ዋልታ) የሱዳን ጦር እና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከማክሰኞ ጀምሮ የ24 ሰዓት የተኩስ አቁም ስምምነት አወጁ፡፡

ስምምነት ላይ የደረሱት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ባደረጉት ግፊት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ስምምነቱ የሰብዓዊ እርዳታ ማድረሻ የሚሆን መንገድ ለማስከፈት ያለመ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

በአገሪቱ አራተኛ ቀኑን የያዘው ግጭቱ የሱዳን ወታደራዊ መሪ ጄኔራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን በሚመሩት የሱዳን ጦር እና ምክትላቸው መሃመድ ሀምዳን ደጋሎ (ሄምቲ) በሚመሩት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል እየተደረገ ይገኛል፡፡

በግጭቱ እስካሁን 200 የሚደርሱ ሰዎች ሕይወት ማለፉ የተነገረ ሲሆን እስከ ትናንት ድረስ ባለው መረጃ 1 ሺሕ 800 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ዘገባዎች አመላክተዋል፡፡