በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እና በአራት ክልሎች የእጩዎች ምዝገባ የካቲት 21 ይጠናቀቃል – ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የካቲት 15/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም በቤኒሻንጉል፣ በሐረሪ፣ በጋምቤላ እና ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልሎች የእጩዎች ምዝገባ የሚጠናቀቀው የካቲት 21 ቀን 2013 ዓ.ም መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

በእነዚህ ከተማ አስተዳደሮች እና ክልሎች የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህንኑ አውቀው ከጊዜ ገደቡ በፊት የእጩዎች ምዝገባ እንዲያጠናቅቁም ቦርዱ ጥሪውን አቅርቧል።

በሌላ በኩል ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የእጩዎች ምዝገባን እያከናወነ እንደሆነ የገለጸው ቦርዱ፣ በዚሁ መሠረት በአዲስ አበባ መስተዳድር የሚገኙ የምርጫ ክልል ቢሮዎችን ዝርዝር የመገኛ አድራሻ ለማግኘት ለሚፈልጉ ፓርቲዎች አድራሻውን ይፋ አድርጓል።

ተጨማሪ አስፈጻሚዎችን ለማነጋገር የሚፈልጉ ፓርቲዎች አድራሻቸውን ከቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሥራ ክፍል መውሰድ የሚችሉ መሆኑን በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ አስታውቋል።