ኦቢኤን ለመተከል ዞን 900 ኩንታል ስንዴ ድጋፍ አደረገ

 

ለመተከል ዞን 900 ኩንታል ስንዴ ድጋፍ

የካቲት 15 /2013 (ዋልታ) – የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ለችግር ለተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች 900 ኩንታል ስንዴ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ እና የኦቢኤን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዝናቡ አስራት ዛሬ በግልገል በለስ ከተማ ተገኝተው አስረክበዋል።

የኦቢኤን ሥራ አስኪያጅ አቶ ዝናቡ አስራት ተቋሙ ከሕዝብ ድምጽነቱ ባሻገር የተቸገሩ ወገኖችን እየደገፈ መሆኑን ገልፀዋል።

ቀደም ሲል በትግራይ ክልል ለተቸገሩ ወገኖች መሰል ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ በመተከል ዞን ለተቸገሩ ወገኖች 900 ኩንታል ስንዴ ድጋፍ ማድረሱን ተናግረዋል።

ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በርካታ ስራዎችን በጋራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በዞኑ ለተቸገሩ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ኦቢኤን በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚነገሩ ጉምዝኛ፣ በርታኛ እና ሽናሽኛ ቋንቋዎች ስርጭት ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁንም ዶክተር ግርማ ጠቁመዋል።

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ እና የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ ለተቸገሩ ወገኖች በአግባቡ ለማድረስ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።