በህወሓት ወታደራዊና ሲቪል አመራሮች ላይ የተመሰረተው ክስ ተቋረጠ

መጋቢት 21/2015 (ዋልታ) በወንጀል ተጠርጥረው ክስ ቀርቦባቸው የነበሩ የህወሓት ወታደራዊና ሲቪል አመራሮች ክስ መቋረጡን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በፌዴራል መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሰረት ከግጭቱ ጋር ተያያዥ የሆኑ ወንጀሎች ተጠያቂነት በተመለከተ ያለውን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በሽግግር ፍትህ ማዕቀፍ ሊታዩ እንደሚገባ ስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል።

ስለሆነም በወንጀል ተጠርጥረው ክስ ቀርቦባቸው የነበሩ የህወሓት ሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮችን ክስ በማቋረጥ ጉዳያቸው በቀጣይ በሽግግር ፍትህ ማዕቀፍ እንዲታይ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ተጠቁሟል፡፡

ስለዚህ በተገለጸው አግባብ ከዚህ ጋር በተያያዘ ክስ ቀርቦባቸው በክርክር ሂደት ላይ ይገኙ የነበሩ የወንጀል ክሶች በአዋጅ 943/2008 አንቀጽ 6 (3) (ሠ) መሰረት የተነሱ መሆኑን የፍትህ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።