መጋቢት 09/2013 (ዋልታ) – በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ሲያዘዋውሩ የተገኙ ስምንት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዞኑ የአስተዳደርና የፀጥታ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሞቱማ ኮርጄ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ተጠርጣሪዎቹ 15 ሽጉጥ ከ2ሺህ በላይ መሰል ጥይቶች ጋር፣ አራት ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ከ849 መሰል ጥይቶች እንዲሁም ሁለት የእጅ ቦምብ ተገኝቶባቸዋል።
16 የወገብ ትጥቆችና 23 የክላሽንኮቭ ጠብመንጃ ካርታዎች በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለም ጠቅሰዋል።
ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ከትናንት በስቲያ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎቹ ከሌላ አካባቢ በተሽከርካሪ በማጓጓዝ በዞኑ አሙሩ ወረዳ አገምሣ ኬላ እንደደረሱ የጸጥታ አካላት ባደረጉት ፍተሻ መሆኑን አስታውቀዋል።
የአሙሩ ወረዳ የፖሊስ አዛዥ ሳጅን ኦላና አብዲሣ በበኩላቸው በተጠርጣሪዎቹ እጅ 119 ሺህ 280 ብር ከባንክ የሂሳብ ደብተር ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸዋል።