አፍሪካ ለዓለም ሰላም መስፈን የድርሻዋን እየተወጣች መሆኑ ተገለጸ

መጋቢት 09/2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ አፍሪካ ለዓለም ሰላም መስፈን የድርሻዋን እየተወጣች መሆኗን በ986ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የበይነ መረብ ውይይት ላይ ገልጸዋል፡፡

ውይይቱ በአፍሪካ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ዙሪያ ያተኮረ መሆኑ ተመላክቷል።

አቶ ደመቀ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በተለያዩ አገራት በሰላም ማስከበር ግዳጅ ላይ  የህይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ያላቸውን ክብር ገልጸዋል።

በዓለም ሰላምና ጸጥታ የማስፈን ዓላማ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ የባለብዙ ወገን መድረኮች መመስረት በምክንያትነት እንደሚጠቀስ በንግግራቸው አውስተዋል።

የሰላም አስከባሪ ኃይል ያሰማሩ አገራት እስከሕይወት መስዕዋዕትነት ድረስ ዋጋ እየከፈሉ መሆኑን ጠቅሰው፣  አፍሪካም ለዓለም ሰላም መስፍን የድርሻዋን እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል።

አያይዘውም ለሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የሚመደበው የፋይናንስና የሎጀስቲክ አቅርቦት መቀነስ የሰላም አስከባሪ ኃይሎች በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው ስራቸውን እንዲያከናውኑ ያስገደደ መሆኑንም አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅትም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘም ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚስፈልግ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ካለው ተጨባጭ ተሞክሮ አኳያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ዙሪያ በሚወጡ ፖሊሲዎችና እቅዶች ወቅት ተሳታፊ ማድረግ ጠቃሚ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በተሻለ ብቃትና ቅልጥፈና ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የተሳተፉ አገራት መካከል የተሻለ ቅንጅት ማድረግ፣ ለአቅም ግንባታ ተግባራት ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ እንዲሁም በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ሴቶች ያላቸውን ልዩ ሚና በመጥቀስ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት ማከናወን እንደሚስፈለግ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመጨመረሻም የአፍሪካ ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ያለባቸውን ተግዳሮቶችን ለመፍታት አፍሪካዊያን የጋራ አቋም በመያዝ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ  በአጽንዖት መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።