በሕንድ ያጋጠመው የኮሮና ቀውስ የቫይረሱን ክትባት ለማዳረስ የሚደረገውን ርብርብ ማጓተቱ ተገለፀ

በሕንድ ያጋጠመው የኮሮና ቀውስ

ግንቦት 09/2013 (ዋልታ) – በሕንድ ባጋጠመው ከፍተኛ የኮሮናቫይረስ ሥርጭት ምክንያት በመላው አለም የቫይረሱን ክትባት ለማዳረስ የሚደረገውን ርብርብ በ140 ዶዝ ወደ ኋላ ማጓጓተቱ ተገለጸ።

ኮቫክስ በተሰኘው ፍትሃዊ የክትባት ማከፋፋያ ጥምረት ሥር ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ክትባት የምታበረክተው ሕንድ የውጪ ንግዷ ላይ በጣለችው ክልከላ ምክንያት ላለፉት ሦስት ወራት አንድም ጭነት መላክ አልቻለችም ነው የተባለው።

ሕንድ ክትባቱን የምታመርተው ሲረም ኢንስቲትዩት ኢንዲያ በተባለ ተቋሟ አማካኝት ሲሆን፣ ኢንስቲትዩቱ በመላው አለም በኮቫክስ ሥር ይሰራጫል ተብሎ ከሚጠበቀው ሁለት ቢሊየን ክትባት ግማሹን ይሸፍናል ተብሎ ነበር።

ሕንድ ለአራት ተከታታይ ወራት ክትባቱን አምርታ ትጭናለች ተብሎ አይጠበቅም። ይህ ከሆነ ጉድለቱ አሁን ካለበት ወደ 190 ሚሊየን ያሻቅባል ነው የተባለው።

የተመድ የሕፃናት ኤጀንሲ ዩኒሴፍ የኮቫክስን ክትባት የመግዛት እና የማከፋፈል ተግባሩን እያከናወነ ሲሆን፣ የቡድን ሰባት እና የአውሮፓ ሕብረት አገራት ከራሳቸው ድርሻ ላይ ክትባቶችን እንዲያካፍሉ እየጠየቀ ይገኛል።

ዩኒሴፍ እንዳለው አገራቱ የዜጎቻቸውን ፍላጎት ካሟሉ በኋላ 153 ሚሊየን ዶዝ ክትባት መለገስ የሚያስችል አቅም አላቸው።

የዩኒሴፍ ኮቫክስ የአቅርቦት አስተባባሪ ጂያን ጋንዲ “ቀጣይ ዶዞች መቼ ይጫናሉ የሚለውን የማናውቅበት ደረጃ ላይ ነው ያለነው” ብለዋል።

“ነገሮች በቅርቡ ተስተካክለው ወደ መስመራችን እንመለሳለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን በሕንድ ያለውን ሁኔታ ለመገመት አስቸጋሪ ነው፤ ይህ ከፍተኛ ስጋት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ዩኒሴፍ ክትባት አዋጡ ካላቸው ኃያላን አገራትም የተወሰኑት ከሕዝብ ብዛታቸው በላይ ብዙ እጥፍ ክትባት አዘዋል። እንግሊዝ፣ ካናዳ እና አሜሪካ ቀዳሚዎቹ ናቸው።

በየካቲት ወር የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አገራቸው የሚተርፋትን ክትባት ለደሃ አገራት ለመስጠት ቃል ገብተው ነበር። ነገር ግን እስካሁን ይህ የሚሆንበትን ጊዜ አልገለጹም።

አሜሪካም በተመሳሳይ ጊዜውን ባታስታውቅም ፈረንሳይ ግን ብቸኛዋ ክትባቶቿን ለመለገስ ቃል የገባች የቡድን ሰባት አገር ናት። ፈረንሳይ ግማሽ ሚሊዮን ክትባት ለመለገስ ቃል ገብታለች ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡