ከ69 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ግንቦት 09/2013 (ዋልታ) – በሀገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች ከሚያዝያ 28 እስከ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ  69 ሚሊየን 215 ሺህ 956 ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የኮንትሮባንድ እቃዎቹ ከሀገር ሊወጡ ሲሉ እና ወደ ሀገር ሊገቡ ሲሉ የተያዙ ሲሆን፣ ወደ ሃገር ሊገቡ ሲሉ የተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች  66 ሚሊየን 744 ሺህ 994  ግምታዊ ዋጋ ሲኖራቸው፤ ሊወጡ ሲሉ የተያዙት ደግሞ 2 ሚሊየን 470 ሺህ 962 ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ናቸው ተብሏል፡፡

አዲስ አበባ ኤርፖርት፣ ሀዋሳ፣ ጅግጅጋ፣ ድሬዳዋ፣ ሞያሌ፣ ባህርዳር፣ ጋላፊ፣ አዲስ አበባ ቃሊቲ፣ ጅማ፣ አዳማ፣ አዋሽ፣ ኮምቦልቻና አሶሳ ደግሞ የኮንትሮባንድ እቃዎቹ የተያዙበት የጉምሩክ ቅርንጫፎች መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡

በሳምንቱ በአዲስ አበባ ኤርፖርት፣ በሞያሌ እና በድሬዳዋ ከፍተኛ የገቢ ኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን፣ 41 ተሽከርካሪዎች ኮንትሮባንድ ጭነው መያዛቸው ታውቋል፡፡

ኮንትሮባንድ እቃዎቹ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች፣ የተለያዩ አልባሳት፣ ምግብ ነክ፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ኮስሞቲክስ፣ ልባሽ ጨርቅና ጫማ፣ መለዋወጫ፣ መድሀኒትና አደንዛዥ ዕፅ፣ የጦር መሳሪያዎች እና ሌሎችንም ያጠቃለሉ መሆናቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡