በሕገ-ወጥ የውጭ ምንዛሬና የወርቅ ንግድን ለመጠቆም የሚያስችልና ወሮታ የሚከፈልበት አሰራር ተግባራዊ ሆነ

ጥቅምት 9/2015 (ዋልታ) በሕገ-ወጥ የውጭ ምንዛሬና የወርቅ ንግድ ላይ የተሰማሩ አካላትን ለመጠቆም የሚያስችልና ወሮታ የሚከፈልበት የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች በዚሁ በተዘጋጀው መመሪያ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የባንኩ የሕግ አገልግሎት ዳይሬክተር መስፍን ጌታቸው መመሪያውን አስመልክቶ ባደረጉት ገለጻ የብር ኖት በሕገ-ወጥ መልኩ ከፋይናንስ ተቋማት ውጭ ማከማቸትና ማዘዋወር፣ በሕገ- ወጥ የወርቅ ግብይትና ዝውውር ላይ መሰማራት፣ በሕገ-ወጥ የውጭ ምንዛሬና ግብይት ላይ መሰማራት በአዋጁ መሰረት የተከለከሉ ናቸው ብለዋል።

ሐሰተኛ የገንዘብ ኖት ሕትመትና ዝውውርም በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ በእነዚህና መሰል የወንጀል ተግባራት የተሰማሩ አካላትን በተመለከተ በአካል፣ በስልክ፣ በኢ-ሜይል፣ በፋክስና በሌሎችም መረጃ የሚተላለፍባቸው መንገዶች ጥቆማ መስጠት የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

በመሆኑም በወንጀሉ ዙሪያ ለመጠቆም የሚያስችልና ወሮታ የሚከፈልበት የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱን አብራርተዋል።

በዚህ ሂደት የጠቋሚዎቹን ደኅንነት ለመጠበቅ የመረጃ ሰጪዎች ሁኔታ በምስጢር የሚያዝ ሲሆን ጠቋሚዎችን ከስጋት ነጻ የሚያደርግ አሰራር መሆኑን ተናግረዋል።

በጥቆማው መሰረት መረጃውን አጣርቶ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ብሔራዊ ባንክ ከፍትህ ሚኒስቴር፣ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እንዲሁም ከፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የተውጣጣ ግብረ-ኃይል በጋራ ይሰራል ብለዋል።

ለጠቋሚዎች የወሮታ ክፍያ አሰራር ተግባራዊ መደረጉን ጠቅሰው፤ ለዚህም ጠቋሚዎች በቅድሚያ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተዘጋጀውን ቅጽ መሙላት የሚጠበቅባቸው መሆኑን አስረድተዋል።

በሕገ-ወጥ ድርጊት ምክንያት የተያዘው ጥሬ ብር፣ የውጭ አገር ገንዘብ ወይም ወርቅ ከሆነ ለጠቋሚው ከተያዘው 15 በመቶ የሚከፈለው ይሆናል።

ከሐሰተኛ ገንዘብ ኖት ሕትመትና ዝውውር ጋር በተያያዘ ደግሞ እንደተያዘው ገንዘብ ዓይነትና መጠን ከ20 ሺህ እስከ 200 ሺህ ብር ወሮታ ክፍያ ይፈጸማል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የለውጥ ማኔጅመንት ዕቅድና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አባተ ምትኩ፤ በዘርፉ የሚስተዋለው ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ እየተባባሰ በመምጣቱ የክትትልና ቁጥጥር ሂደቱ መጠናከር ያለበት መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ዙሪያ በተለይም መገናኛ ብዙኃን የሕብተረሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ፣ መረጃ መስጠትና የወንጀሉን አስከፊነት በማስገንዘብ በትኩረት መሥራት አለባቸው ብለዋል።