በመቐለ ከተማ ትምህርት የካቲት 1 እንደሚጀመር ተገለጸ

በትግራይ ክልል በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ እና በኮሮና ምክንያት በመቐለ ከተማ ተቋርጦ የነበረው ትምህርት የካቲት 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚጀመር የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ።

የመቐለ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አታክልቲ ኃይለስላሴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ በከተማዋ በመጀመሪያ በኮሮና ምክንያት በኋላም በህግ ማስከበር ዘመቻው ምክንያት ትምህርት ተቋርጦ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት የከተማዋ ሰላምና ጸጥታ የተረጋጋ በመሆኑና የኮሮና ቫይረስ መከላከል ጥንቃቄን ተግባራዊ በማድረግ በሁሉም ደረጃ ባሉ የትምህርት ክፍሎች ከየካቲት 1 ቀን 2013 ዓ.ም ትምህርት መስጠት ይጀመራል ነው ያሉት።

ወላጆች ልጆቻቸውን ከተጠቀሰው እለት ጀምሮ ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩም አቶ አታክልቲ ጥሪ አቅርበዋል።

በአሁኑ ወቅት በመቐለ ከተማ የሚገኙ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መደበኛ ስራቸውን እያከናወኑ መሆኑንም አስታውቀዋል።