በመተከል ዞን ማረሚያ ቤት በተደረገ ጉብኝት ከሁለት ዓመታት በላይ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ተጠርጣሪዎች ተገኙ

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ኃይል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ማረሚያ ቤት ባደረገው ጉብኝት ከሁለት ዓመታት በላይ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ተጠርጣሪዎችን አገኘ።

ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያቸው ታይቶ በሶስት ቀናት ውስጥ እልባት እንዲሰጣቸውም ግብረ ሃይሉ አሳስቧል።

ግብረ ሃይሉ በማረሚያ ቤት ባደረገው ጉብኝት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በነበረ የፀጥታ ችግር በወንጀል ተጠርጥረው እስካሁን ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ተጠርጣሪዎችን አግኝቷል።

ከፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከሁለት ዓመት በላይ በማረሚያ ቤት መቆየታቸውንም አረጋግጧል።

በግብረ ኃይሉ የህግ ማስከበርና የፀጥታውን ዘርፍ በበላይነት የሚመሩት ሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከሁለት አመታት በላይ መታሰራቸው ከህግ አግባብ ውጪ መሆኑን ገልጸዋል። “በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያቸው ታይቶ በሶስት ቀናት ውስጥ እልባት ሊሰጣቸው ይገባል” ብለዋል።

በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ጉዳያቸው ታይቶ ውሳኔ እንዲያገኙ ግብረ ሃይሉ አሳስቧል።

ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያቸው እየታየ ዋስትና የሚሰጣቸው ካሉ የዋስትና መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባልም ብለዋል።

በዚህም ከፌደራል ዐቃቤ ህግ መርማሪ ቡድን ጋር ስራውን የሚመራ ኮሜቴ ተቋቁሞ በሚቀጥሉት ሶስት ቀናት ውስጥ ለማጠናቀቅ እያጣራ መሆኑን ገልጸዋል።

ግብረ ኃይሉ በዞኑ ህግ የማስከበርና በወንጀል የተጠረጠሩ አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሁኑና የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው እርዳታ እንዲያገኙ እየሰራ መሆኑን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።