በመተከል ዞን እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር እርምጃ የታጠቁ ሃይሎች እጃቸውን እየሰጡ ነው

 ሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር እርምጃ በርካታ የታጠቁ ሃይሎች እጃቸውን ለጸጥታ ሃይሉ እየሰጡ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ኃይል አስታወቀ።

የህግ ማስከበርና የፀጥታውን ዘርፍ በበላይነት የሚመሩት ሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ የጥፋት ቡድኑ በመተከል ዞን በተለይም ቡለንና በቆጂ ወረዳዎች ዜጎችን በመግደል፣ ንብረት የመዝረፍና የማቃጠል አረመኔያዊ ተግባር መፈፀሙን አስታውሰዋል።

የተጠናከረ ዘመቻ በማካሄድ በአካባቢው ህግ በማስከበር ሰላምን ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት በርካታ የታጠቁ ሃይሎች እጃቸውን እየሰጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ታጣቂ ቡድኑ ቀደም ሲል የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ ስጋት አድሮባቸው መኖሪያቸውን ለቀው የነበሩ ዜጎችም ወደ ቀያቸው እየተመለሱ መሆኑን ሌተናል ጀኔራል አስራት ገልጸዋል።

ግብረ ሃይሉ አካባቢውን ከተረከበ በኋላ በተለይ ስጋት ተፈጥሮባቸው የነበሩ አካባቢዎችን በማረጋጋት ወደ ተሻለ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል።

በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪና የኮማንድ ፖስቱ የፖለቲካና ህዝባዊ ውይይቶች መሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በዜጎች ላይ ጥቃት የፈፀመውን ታጣቂ ቡድን የማደን ስራ መቀጠሉን ገልጸዋል።

የተፈፀመውን ጥቃት በመምራትና በማስተባበር የተጠረጠሩና ጥቃቱን መከላከል ሲገባቸው ሃላፊነታቸውን ያልተወጡ አመራሮች ላይ ህጋዊና ፖለቲካዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ተስፋዬ በልጅጌ

የጥፋት ቡድኑን አላማ ያልተቀበሉ የጉሙዝ ማህበረሰቦችን ጨምሮ በተለያዩ የማህበረሰብ አካላት ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወትማጥፋት፣ አካል ማጉደልና ንብረት ማውደም መፈፀሙን አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል።

ችግሩ እኩይ አላማ ያላቸው ሃይሎችን ብቻ የሚመለከት መሆኑን ጠቅሰው፤ “በዘላቂነት መፍትሄ ለማበጀት ግብረ ሃይሉ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው” ብለዋል።

ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ የማድረስና ወደ ቀዬአቸው መልሶ የማቋቋም ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አቶ ተስፋዬ ገልፀዋል።

በሂደቱ የሰላምና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ህዝባዊ ውይይቶች እንደሚካሄዱም ተናግረዋል።

(ምንጭ፡-ኢዜአ)