በመተከል የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም 50 ሚሊዮን ብር ገቢ የማሰባሰብ እንቅስቃሴ ተጀመረ

 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም 50 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ባበክር ከሊፋ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ በመተከል የጸጥታ ችግር ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ተፈናቃዮችን ለመደገፍ እና መልሶ ለማቋቋም ዕቅድ አዘጋጅቶ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

እቅዱን ለማሳካት በየደረጃው ኮሚቴዎች መቋቋማቸውን ጠቁመው፤ “በአሶሳና ካማሽ ዞኖች እንዲሁም ማኦኮሞ ልዩ ወረዳና አሶሳ ከተማ አስተዳደር ህብረተሰቡን ማወያየት ተጀምሯል” ብለዋል፡፡

ባለሃብቶች፣ የመንግስት ሠራተኞች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎች የህብረተሰቡ ክፍሎች ድጋፉ ከሚሰበሰብባቸው መካከል እንደሚገኙበት አስረድተዋል፡፡

የገቢ ማሰባሰብ እቅዱ በሚቀጥሉት 15 ቀናት ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡ ድጋፉ በዓይነት ጭምር እንደሚሰበሰብ አቶ ባበክር ገልጸው፤ በአጠቃላይ 50 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማድረግ መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡