በመዲናዋ በአንድ ጀምበር ከአንድ ሚሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል የተያዘውን መርኃግብር ተጀመረ

ሐምሌ 04/2013 (ዋልታ) – በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ጀምበር ከአንድ ሚሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል የተያዘው መርኃግብር ከማለዳው አንስቶ ተጀምሯል።

መርኃግብሩን ያስጀመሩት የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ በመዲናዋ በአንድ ጀምበር ከአንድ ሚሊየን በላይ ችግኝ ይተከላል ብለዋል።

የአዲስ አበባ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላን በአራት ኪሎ ቤለር ሜዳ ያስጀመሩት ምክትል ከንቲባዋ፣ መርኃግብሩ በመዲናዋ አስራአንዱም ክፍለ ከተሞች እንደተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ነዋሪዎችም ብርድና ዝናብ ሳይበግራቸው በማለዳው ተገኝተው የችግኝ ተከላውን አከናውነዋል።

በ2013 በአዲስ አበባ 7.5 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል እቅድ የተያዘ ሲሆን፣ እስካሁን 5.1 ሚሊየን ችግኝ መትከል እንደተቻል ወ/ሮ አዳነች አበቤ ገልፀዋል።

የተተከሉ ችግኞችን ለማፅደቅም የህብረተሰቡ እንክብካቤና ጥንቃቄ እንዳይለየው መልዕክት ተላልፏል።

(በደምሰው በነበሩ)